ስለእኛ

Printer-friendly version
የዚህ ድርጅት/ማህበር ድምር ውጤት የሚገለፀው ሁላችንም ማህበራዊ ኃላፊነታችንን ስንወጣ ነው፡፡ የልጅነት ዘመናችንን ያሳለፍንበት ማህበረሰብና በወጣትነት ዘመንም የምንጠራበት «የኮረም ልጆች» የሚለው መጠሪያችንን ዳግም እውን ለማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታችንን በያለንበት መወጣት ይገባናል፡፡ የእኛ ሃሳብና ዓላማ የማህበረሰባችንን ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ እንደ አንድ ትልቅ የቤተሰብ አባል መስራት ነው፡፡

የዚህ ድርጅት መሰረት የተጣለው እ.ኤ.አ ሃምሌ4/ ቀን 2008/ እንደ ኢትዩጵያውያን አቆጣጠር ደግሞ ሰኔ27 ቀን2000 ዓ/ም በጥቂት ግለሰቦች አነሳሽነት ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የተሰበሰቡት የቀድመውን ለማስታወስ፣ የአሁኑን ለማየት ሲሆን ራሳቸውን ደግሞ ያሳደገንን ማህበረሰብ ህይወት ለመለወጥ እስከ አሁን ምን ሰራን የሚል ጥያቄ በመጠየቅ ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በትዝታ ወደ ኋላ ተመልሰው ያሳደጋቸው ማህበረሰብ ባህልና እሴት በማስታወስ «እንችላለን፣ እናደርጋለንሜ የሚለው የወጣትነት ዘመን ወኔያቸውን ስንቅ አድርገው በሚከተሉት መሰረታዊ ዓላማዎች የተሰባሰቡ ናቸው፡፡

  1. በኮረምና አካባቢዋ ተወላጆችና ደጋፊዎች መካከል ያለውን የመራራቅ ክፍተት በመሙላት ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር መፍጠር ነው፡፡ ይህ ያስፈለገበት ምክንያት ግንኙነታቸው የላላ ግለሰቦች፡ ቤተሰቦችና ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች በማቀራረብ የኮረምና አካባቢዋ ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ለማሟላት አቅም በፈቀደ መጠን እንዲያግዙ ለማድረግ ነው፡፡
  2. የአንድነትና የትብብር ስሜት በመፍጠር የአካባቢ፣ የንዑስ አካባቢና የሌሎችን የጋራ ዓላማ በጋራ ለማስፈፀምና ለመስራት ተነሳሽነትና ፍላጎት እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡
  3. የኮረምና አካባቢዋ ማህበረሰብ ፍላጎትን ለመረዳት፣ ማህበረሰባችን በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የሚያጋጥመውን የኢኮኖሚ ችግር መፍትሄ ለማፈላለግ ሃብትን በማስተባበር የተመረጡ ኘሮጀክቶች በመስራት ረገድ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣትና ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን ነው፡፡

የእኛ ድርጅት ከፓለቲካ ነፃ የሆነ ነው፡፡ ከማንኛውም የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የፓለቲካና የማህበራዊ ጉዳይ በተለየ ሁኔታ ግንኙነት የሌለው ነው፡፡ የእኛ ግብ የማህበረሰባችን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ሁሉ የመፍትሄ ቋቶች ለመሆን ሳይሆን በጉዳዩ ዙሪያ ፍላጎት ካላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተባብረን ውጤት ያለው ስራ በትምህርት፣ በጤናና ዘላቂ ኢኮኖሚ ልማት የሚኖርበት ሁኔታ ለማመቻቸት ነው፡፡

ለስኬታችን ወይም ለውድቀታችን ዋና መንስዔ ወይም መሰረት ተባብረን የመስራት ችሎታችንና ብቃታችን ነው፡፡ የእኛ ትኩረት የተጠኑና የታቀዱ ዓላማዎችን እውን ለማድረግ እጅግ ብዙ የማይባል እውቀትና የስራ ፍልስፍና ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ከእኛ ጋር አብረውን ለሚጓዙና አስተያየታቸውን ለሚሰጡን እንዲሁም ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ለሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች የላቀ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ ስለዚህ እርስዎም የማህበረሰባችን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ በምናደርገው ጉዞ አብረውን እንዲጓዙና የበኩልዎን ድርሻ እንዲወጡ እንጠይቃለን፡፡ የያዝናቸውን የተቀደሱ ዓላማዎች ተግባራዊ ለማድረግና ውጤት ለማምጣት የእርስዎ አስተዋፅኦ ወሳኝነት አለው፡፡

ራዕያችን ግቡን የሚመታውና የምንሰራው ስራ ውጤት የሚያመጣው ባለን ቀና የበጎ ፍቃድ አገልግሎትና ላደግንበት ማህበረሰብ የባህል እሴት በምንሰጠው ክብርና በሚሰማን ኃላፊነት ነው፡፡ ወልዶ በሳደገን፥ አስተምሮ ለቁም ነገር ባበቃን፥በኮረምና አካባቢው ማህበረሰብ ላይ ሊኖረን የሚገባውን ኩራትና ባለ ውለታነታችንን በማስታወስ የጋራ ሀላፊነታችንን ያስገነዘቡንን ግለ-ሰቦች እጅግ እያመሠገንን የሚመለከታቸው አንባቢያንም በኮረምና አካባቢው ተራ ህዝብ ኑሮ ላይ አወንታዊ ለውጦችን ለማምጣት በጀመርነው ጉዞ እንድትቀላቀሉን በአክብሮት እንጋብዛችሁዋለን። እዚህ ላይ ማስታወስ የምንፈልገው ድርጅታችን የሚንቀሳቀሰው በአባላት በጎ ፈቃድና ውዴታ እንዲሁም መጠነ ሰፊ በሆነ የግል መስዋዕትነት እንደመሆኑ መጠን ይህንን ራዕይ ለመተግበር ቀላል ሥራ አለመሆኑን ነው። ራዕያችን እዉን ሊሆን ግን ይችላል። ሌሎች ስላልሠሩት ሥራ አናስብ፥ አሁን ወሳኙ እኛ የምንሠራው ነውና! ከታሪካዊ ሃላፊነታችን ለመራቅ ምክንያት አንስጥ!


«የኮረም ልጆች» የሚለው ሐረግ ትርጉሙ የዘር፥ የሀይማኖት፥ የፖለቲካ ወይም፥ የጾታ ልዩነትን አያመለክትም። ኮረም ተወልደው ያደጉትን፥ ሌላ ቦታ ተወልደው ኮረም ያደጉትን ወይም የተማሩትን እንዲሁም ከሌላ ቦታ በመምጣት ኮረም በመምህርነት ወይም በሌላ ሙያ የሰሩትን ሁሉ ያጠቃልላል።